Tuesday, 22 December 2015

አወዛጋቢው የመውሊድ በዓል


በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
 ምስጋና ሁሉ ለአለማት ጌታ አላህ የተገባ ይሁን፡፡ የአላህ ሰላምና እዝነት የሰውን ልጅ ከመሃይምነት ፅልመት ወደ ኢማን ብርሃን ሊያወጡ በተላኩት የነብያት ሁሉ መደምደሚያና መቀምቀሚያ በሆኑት ነበያችን፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸውና የነሱን ፈለግ በተከተለ ላይ ሁሉ ይስፈን፡፡  ነብያችንን ከነፍሳችን ከልጆቻችን ከወላጆቻችን እንዲሁም ከሰዎች ሁሉ አስበልጠን መውደድ እንዳለብን በተመለከተ የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ከወላጆቹ ከልጆቹ ከሰው ሁሉ ይበልጥ እርሱ ዘንድ ተወዳጅ እስክሆን ድረስ አንዳችሁም አላመነም” ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
 መልዕክተኛውን መውደድ በተመለከተ እጅግ በጣም ብዙ አያቶች በቁርአን ላይ የሰፈሩ ሲሆን ለአብነት በሱረቱል ተውባ አንቀጽ ቁርጥ 24 ላይ የተጠቀሰውን መመልከት ይቻላል፡፡
 “በአባቶቻችሁ እና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ ሚስቶቻችሁም፣ ዘመዶቻችሁም የሰበሰባችኋቸው ሀብቶችም መክሰሯን የምትፈሯት ንግድም የምትወዷቸው መኖሪያዎችም በእናንተ ዘንድ ከአላህ እና ከመልዕክተኛው በእርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደሆኑ አላህ ትእዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ በላቸው አላህም አመፀኛ ህዝቦችን አይመራም፡፡” (ተወባህ 24)  ታዲያ ግዴታ ከሆነው የረሱልን መውደድ ውስጥ የተወለዱበትን ቀን ማክበር ይገኝበታል ወይስ አይገኝበትም? በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ሰዎች ይወዛገባሉ፡፡ በእስልምና ውስጥ መውሊድ የሚባል አመት በዓል አለ ወይስ የለም እያሉ ይከራከራሉ፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶም ብዙ ቃሎች ይሰነዘራሉ መፅሐፎች ይፃፋሉ፡፡ በራሪ ወረቀቶችም ይበተናሉ አያሌ ድርጊቶች ይከናወናሉ እውነታው ምን ይሆን የአንዳንድ ሐቅ ፈላጊ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡

እውነተኛ ውዴታ በተግባር ይገለፃል

  አላህንና መልዕክተኛውን መውደድ ግዴታ ነው አላህንና መልዕክተኛውን የማይወድ አማኝ አይደለም (የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነው አይባልም)፡፡ ውዴታው የሚገለፀው የነብዮን ፈለግ ሱና በመውደድና በመከተል ትእዛዛቸውን በመተግበር የከለከለሉትንና ያስጠነቀቁትን ነገር በመገፍተርና ፈጠራ ነገሮችን በመወርወር ነው፡፡
  የነብዩ ወዳጅ ሁልጊዜ ለሳቸው ታዛዥ ነው አያምፅም መመሪያቸውን አይጥስም ያልታዘዘውን አይሰራም አላህ እንዲህ ይላል
 “አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ አላህ ይወዳችኋልና ኃጢያቶቻችሁን ለእናንተ ይምራልና አላህም መሐሪ አዛኝ ነው በላቸው፡፡” አል ዒምራን 31
  ኢማሙ ሐሰን አል በስሪ (አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) እንዲህ ይላሉ “ሰዎች ነብዩን እንወዳለን እያሉ ሲሞግቱ አላህ በዚህች አንቀጽ ፈተናቸዉ፡፡”
  ነብያችንን የሚወድ ሰው እሳቸውን ይከተላል የሰሩትን ይሰራል የተውትንም ይተዋል ኢማሙ ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሱል እንዲህ ብለዋል “ የእርሱን ፈለግ የሚይዙና ትዕዛዙን የሚከተሉ ረዳቶች እና ጓደኞች ከህዝቦች አድርጐለት እንጂ አላህ ነብይን አልላከም ከዚያም ከነሱ በኃላ የማይሰሩትን የሚናገሩ ያልታዘዙትን የሚሰሩ ይተካሉ (እነዚህን) በእጁ የታገላቸው (የተጋደላቸው) ሙእሚን ነው፡፡ በምላሱም የታገላቸው ሙእሚን ነው ከዚህ በኃላ የሰናፍጭ ፍሬ ያህል እንኳ ኢማን የለውም፡፡”
  ያልታዘዙትን የሚሰሩትን አስመልክቶ የታገላቸው ሙእሚን ነው ማለታቸው የእሳቸው ትዕዛዝ የሌለበትን ነገር ምንም እንኳ ጥሩ መስሎ ቢታየንም ልንሰራው እንደማይገባ ያስረዳናል፡፡ ቡኻሪና ሙስሊም ከሙእሚኖች እናት አዒሻ በዘገቡት ሀዲስ ነብዩ እንዲህ ብለዋል “ ትዕዛዛችን የሌለበትን ስራ የሰራ (ስራው) ተመላሽ ነው፡፡”
ልብ ያለው ልብ ይበል
ነብያችንን መውደድ ግዴታ መሆኑ ይታወቃል እውነተኛ ውዴታ በተግባር ይገለፃል፡፡ ማንኛውም የቢድዓ ተግባር ጥመት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ታዲያ ይህ እንዲህ ከሆኑ ነብያችን የተወለዱበትን ቀንን ማክበር ውዴታ ነው ወይስ ጥላቻ? ሱና ነው ወይስ ቢድዓ? ከእምነት ነው ወይስ ከባህል? በሚቀጥለው ርዕሳችን የምናየው ነጥብ ነው፡፡

ውዴታ ነው ወይስ ጥላቻ

መውሊድ የሚያከብሩ ሰዎች መውሊድን የሚያከብሩት ነብዩ ወደው ነው ወይስ ጠልተው ? አላህን
መገዛት ነው ወይስ አላህን ማመፅ? ነብዩን ወደው አላህን እየተገዙ ከሆነ ታዘው ነው ወይስ ሳይታዘዙ? ታዘው ከሆነ ይህን ትዕዛዝ ነብያችን ለህዝባቸው አብራርተውታል ወይስ አላብራሩትም? አብራርተውታል ከሆነ የት አለ? ከቁርአን ከሀዲስ? ደብቀውታል አላብራሩትም ከሆነ ነብዩን መልዕክታቸውን አላደረሱም ማለት ነው ይህ ደግሞ የማያጠራጥር ክህደት ነው፡፡
 “አንተ መልዕክተኛ ሆይ ከጌታህ ወደ አንተ የተወረደውን አድርስ ባትሰራም መልዕክቱን አላደረስክም አላህም ከሰዎች ይጠብቅሃል አላህም ከሃዲዎችን ሕዝቦችን አያቀናም፡፡” አል ማኢዳህ 6-7 
 ኢባዳ ላይ አላህና ረሱል ከደነገጉት ውጭ ምንም አይነት ድንጋጌ የለም ማንም ሰው በዘፈቀደ እንደፈለገ ሊወስንና ሊደነግግ አይችልም ይህን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፡-
“ከሃይማኖት አላህ በርሱ ያልፈቀደውን ለነርሱ የደነገጉ ተጋሪዎች ለነርሱ አሏቸውን? የፍርዱ ቃል ባልነበረ ኑሮ በመካከላቸው (አሁን) በተፈረደ ነበር በደለኞችም ለነርሱ አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ አላቸው፡፡” አል ሹራ
21
የነብያችንን የልደት ቀን ማክበር እውነታው ምን ይሆን?
የነብዩን የልደት ቀን ማክበር ከእምነት ነው ወይስ ከባህል? ከእምነት ነው የሚል ካለ ማስረጃ ያምጣ ምክንያቱም ያለምንም ማስረጃ ሃይማኖት ውስጥ አንዳችም ስራ መስራት ስለማይቻልና ስለማይፈቀድ ነው፡፡ የመውሊድ በዓል ከቁርአንና ከሀዲስ መሰረት አለው ብሎ መድከም ከንቱ ነው፡፡ መውሊድ በነብዩ የሕይወት ዘመን ፈፅሞ እንዳልነበር አይደለም ዑለማዎች ጃሂሎች (መሃይሞች) የሚያውቁትና የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ መውሊድ የሚያከብሩት ሳይቀሩ የማይክዱትና የማያስተባብሉት ተግባር ነው፡፡ የመልዕክተኛው ፈለግ የሌለበት ተግባር ደግሞ ወደ አላህ መቃረቢያ የረሱል ውዴታ መገለጫ መንገድ ሊሆን እንደማይችል የማንም ሰው ስምምነት ነው፡፡ ታዲያ መውሊድ ማክበር እንደ እምነት ምሶሶ ተደርጐ የሚቆጠረው ለምንድን ነው?  መውሊድ ከሃይማኖት ቢሆን ኑሮ ነብዩ ይሰሩት ነበር ስለ አከባበሩ ስነ ስርአት ያስተምሩ ነበር ባልደረቦቻቸውም ይከተሏቸው ነበር በየአመቱ ይፈፅሙት ነበር እነሱ ከእኛ የበለጠ ነብዩን ይወዳሉ፡፡ ትዕዛዛችን ያከብራሉ የነብዩን ሱና ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እምነትንም በተገቢው ሁኔታ ከእኛ በበለጠ መልኩ ይረዳሉ እነሱ የተውትን ተግባር የማያውቁትን ነገር ፈጥሮ አምጥቶ ከሃይማኖት ነው ማለት ከምን የመጣ ነው?
 እንደሚባለው የተወለዱበትን ቀን ማክበር ከእምነት ቢሆን እሳቸው ባብራሩትና ባስተማሩት በህይወታቸው እያሉ አንዴም እንኳ ቢሆን ባከበሩትና ባስተማሩት እሳቸው ከሞቱም በኃላ ባልደረቦቻቸው በሰሩት ነበር ይህ አለመሆኑ በሳቸው አለመነገሩም ሆነ አለመተግበሩ ከእስልምና አለመሆኑን በግልፅ ያብራራል፡፡
 ሐቅ ለፈለገ ሰው ስለመውሊድ አፈፃፀምና ስነ-ስርአት ቢመለከት እውነታው ይገለፅለታል፡፡ የዲናዊ በዓሎች ድንጋጌያቸውንና የአፈፃፀም ስነ ስርአታቸውን ከዲናዊ የመረጃ ምንጨች የምናገኝ ሲሆን ስለመውሊድ አከባበር ግን ከነአካቴውም ምንም አልተገለፀም፡፡ እንደ አረፋና ፊጥር በዓል ሰላት ተክቢራና ሌሎች ዒባዳዎች ፈፅሞ እንዳላሉት አይዘነጋም፡፡  በሀገራችን የመውሊድ ቀን መለያየቱ ሳንገነዘበው ማለፍ የሌለብን ነገር ቢሆንም ነብያችን የሞቱት ረቢዓል አወል አስራ ሁለተኛው ቀን ሰኞ እለት ሲሆን የተወለዱበት ቀን ግን ሰኞ እለት ይሁን እንጅ ስንተኛው ቀን በየትኛው ወር በሚለው ዘገባ ላይ የታሪክ ምሁሮች ይለያያሉ፡፡ ረቢዓል አወል ወር ዘጠነኛው ቀን ተወለዱ የሚለውን ትክክለኛ የሆነ ሰነድ በመጥቀስ ብዙሃኑ የታሪክ ምሁራን ያፀድቃሉ፡፡
የዒደል አድሃን (አረፋን) እና የዒደል ፊጥርን በአል ብንመለከት የራሳቸው የሆነ ህግና ደንብ አላቸው እንደየእውቀቱ መጠን ቢለያይም ማንም ሙስሊም ያውቀዋል፡፡ በዑለሞች ዘንድ ግን በስፋት ይታወቃል በመፅሃፋቸው ላይ ተመዝግቦ ይገኛል የትም ቦታ አይለያይም ስለመውሊድ ግን ማወቅ ብትፈልግ የአንድ መስጅድ የመውሊድ ገንዘብ ሰብሳቢ ኮሚቴዎችን አስተማሪ መምህሮችን እንዴት እንደሚከበር ብትጠይቃቸው ሊነግሩህ አይችሉም ምክንያቱም መውሊድ የራሱ የሆነ ህግና ደንብ ወግና ስርአት ስለሌለው ነው፡፡
 መውሊድ ኹጥባ አለውን? አዛንስ? ሰላትስ? ካለው ሰላቱ ይቀድማል ወይስ ኹጥባው? ደቤው ይቀድማል ወይስ መንዙማው? ጠይቋቸው ምንድነው መልሳቸው?
1.       ነብዩን መውደዳችንን ለመግለፅ ነው እሳቸውን ለማስታወስ ነው ምን ችግር አለበት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አንደኛ፡- ነብዩን መች ረስተናቸው ነው በአመት አንድ ቀን የምናስታውሳቸው? አመቱን በሙሉ የረሳቸው ካለ በአመት አንድ ቀን ሊያስታውሳቸው የሚፈልግ እምነቱን ይፈትሽ፡፡ ነብያችን እሳቸውን ለማስታወስ ብሎ በአመት አንድ ቀን መውሊድ የሚያከብርን ሰው አይፈልጉም ምክንያቱም አላህ ስማቸውን ከስሙ ጋር አቆራኝቶ እሱ በተጠራበትና በተወሳበት ሰአትና ቦታ እንዲጠሩና እንዲወሱ አድርጓል በአል ሸርህ ሱራ አራተኛ አያት ላይ  “መወሳትክንም ላንተ ከፍ አድርገንልሃል” ብሏል በአዛንና በኢቃማ በኹጥባ እንዲሁም በተለያዩ ትምህርቶችና ዚክሮች ላይ አላህ ከተወሳ በኃላ እሳቸው ይወሳሉ ይህ ደግሞ እሳቸውን ለማውሳት ይበቃል ውዴታቸውን ያስገኛል፡፡
ሁለተኛ፡- የነብዩ ውዴታ የሚገለፀው በአመት አንዴ ተሰብስቦ በመብላት በመጠጣት በመጨፈር በመደለቅ ወይም በመቃም መንዙማ በማዳመጥ አይደለም፡፡ ውዴታ የሚገለፀው ያዘዙትን በመታዘዝ የከለከሉትን በመከልከል ፈጠራን ቢድዓን በመገፍተር ሱናን በመከተል እሳቸው የሰሩትን ስራ በመተግበር ነው፡፡
2.       ንያችን ጥሩ ከሆነ አላማችን ቅንና ያማረ ከሆነ ቢድዓ ቢሆንስ ምን ችግር አለበት፡፡ ለምንድ ነው የምታከሩት የአንዳንድ አባቶች አባባል ነው፡፡ ይህ አባባል አታላዬች የሚያታልሉበት ሞኞች የተሸወዱበት የዋሆች የተሞኙበት ውድቅ አባባል ነው፡፡ 
 መልሱም አንድ መጥፎን ስራ ጥሩ ንያ ሊያስተካክለው አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ እንግዳ የመጣበት ሰው እንግዳ ማክበር ዋጅብ ነው ብሎ እንግዳ ለማክበር በጥሩ ንያ ባማረና በተቀደሰ ሃሳብ ቢስማላሂ አላሁ አክበር ብሎ ውሻ ቢያርድ የሰውዬው ጥሩ ንያ የእንግዳ ማክበር ግዴታነቱ በአላህ ስም መታረዱ የውሻን ስጋ ሀላል አያደርገውም ምክንያቱም የውሻ ስጋ በመሰረቱ ሀራም ስለሆነ፡፡ እንደዚሁም በጥሩ ንያ ተብሎ ቢድዓ የሆነው መውሊድ ቢከበር ጥሩው ንያ ቢድዓውን ሱና አያደርገውም ሀራሙን ነገር ሀላል እንዳላደረገው ሁሉ ልብ ያለው ልብ ይበል ተናጋሪ አስተውሎ ይናገር፡፡ 

መውሊድ የቢድዓ በዓል ብቻ መች ሆነ

መውሊድ በራሱ መጥፎ ፈጠራ ከመሆኑ ባሻገር እጅግ በጣም በርካታ እንከኖችና የተወገዙ ተግባሮች ሲፈፀሙበት ይስተዋላል፡የተፈቀደ በዓል ቢሆንም እንኳ ወንድና ሴት በመቀላቀል በድቤ በጭብጨባና በጭፈራ ማክበር በኢስላም አይታወቅም፡፡ እንዲያውም ከቀድሞዎቹ የመካ ሙሽሪኮች አምልኮ ጋር የሚያመሳስል ውግዝ ተግባር ነው፡፡ ይህም በቁርአን ተወስቷል “በቤቱ ዘንድም (በካዕባ) ስግደታቸው ማፏጭትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም”
 በመውሊድ በዓል በአብዛኛው የተለያዩ የሽርክ ተግባራት ይፈፀማሉ፡፡ እንዲሁም ይዘቱ እየሰፋና ከቀብር አምልኮ ጋርም እየተሳሰረ መጥቷል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የቀብር አምልኮዎች መውሊድ በሚል ስያሜ የሚተገበሩ ናቸዉ፡፡ በሀገራችንም የእነ ሸይኽ እገሌ መውሊድ እየተባለ ወደ ተለያዩ ሩቅ ስፍራዎች ጉዞዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ስለት፣ ዱዓእ፣ እርድና የመሳሰሉ የኢባዳ ዘርፎች ሁሉ ለፍጡራን ይቸራሉ፡፡ በሱረቱልኑርአንቀጽ 63 እንደተገለፀው የነብዩን ትዕዛዝ መጣስ ለከፋ ችግር ያጋልጣል ለመሆኑ በእንዲህ ያለ ተግባሮች የተሞላ መድረክ በየትኛው ሚዛን ሲለካ ነው ጥሩ ፈጠራ የሚባለው፡፡
 ብዙ ጊዜ መውሊድ ሲከበር በሐሰት የተሞሉ ትምህርቶች ተቀባይነት ሌላቸው መውዱዕ ሀዲሶች ድንበር ማለፍ ያለባቸው፡፡ ውዳሴዎች ይሰማሉ እያሉ ከአላህ ውጭ ያሉ ፍጡሮችን መጣራት በእነሱ መመጀን ነበዩን ከጭንቀት እንዲያላቅቋቸው መለመን በሽተኞቻቸውን እንዲያድኑላቸው መጠየቅ እንዲሁም በአጠቃላይ ከአላህ በስተቀር ማንም ሊተገብራቸው የማይችሉትን ተግባራት ነብዩን እና ሌሎችን የአላህ ደጋግ ባሪያዎች መጠየቅ ይገኙበታል፡፡  ይህንን አስመልከቶ አላህ ለመልዕክተኛው እንዲህ ይላሉ 
 “እኔ ለናንተ ጉዳትንም ቀጥታንም አልችልም በላቸው፡፡” አልጅን 21  ነብያችን በዚህ መውሉድ ይሳተፋሉ ይመጣሉ ብለው የሚያስቡት ለሳቸው ብለው የሚነሱት ሰንደል የሚለኩሱት አድሩስ የሚያጨሱት ጉዝጓዝ የሚጐዘጉዙት በርካታ ቁጥር እንዳላቸው አይዘነጋም፡፡  ይህ መጥፎ ሃሳብና አስፀያፊ ተግባር ከመሃይምነት የመነጨ ማስረጃ የሌለው ተግባር ነው፡፡ ነብዩ ከሞቱ በኃላ ከማንም ሰው ጋር አይገናኙም በቂያም ቀን በፊት ከቀብር አይወጡም በዚህ የፈጠራ ስብስብ ላይ አይሳተፉም፡፡ ለዚህም ማስረጃው በሱረቱል ሙእሚን አንቀጽ ቁጥር 15 እና 16 የተጠቀሰው የአላህ ሱ.ወ ቃል ነው፡፡
“ከዚያም እናንተ ከዚህ በኃላ በእርግጥ ሟቾች ናችሁ ከዚያም እናንተ በትንሳኤ ቀን ትቀሰቀሳላችሁ፡፡”
ከሞት በኃላ የትንሳኤ ቀን ሳይደርስ የሚቀሰቀስ ላለመኖሩ አላህ ተናግሯል በቁርአን ውስጥ አብራርቷል፡ ፡ ከዚህ በኃላ መደናገርም ሆነ ማደናገር መምታታትም ሆነ ማምታታት አያስፈልግም ነብዩ በሀዲሳቸው የትንሳኤ ቀን የመጀመሪያው ሰው ተቀስቃሽ መሆናቸዉን ተናግረዋል፡፡
 በመውሊድ ቀን  የተከለከሉና የተወገዙ መንዙማና ሀድራዎች ይቀርባሉ፡፡
ስለ መውሊድ ጥሩ ጎን ነው ያላችሁትን ትናገራላችሁ በጣም ብዙ የከፋ ተግባሮችን ግን ትደብቃላችሁ እስከ ሽርክ የደረሱ ወንጀሎች እየተፈፀሙበት መሆኑን ከላይ ለማየት ሞክረናል ቅድሚያ ሰጥታችሁ ማየት ያለባችሁ ካመጣው ጥቅም ይልቅ ያሰረፀውን ጉዳት ነው ምክንያቱም ዑላማዎች ያፀደቁት አንድ መርህ አለ፡፡ 
“ጥሩውን ነገር ከማምጣት መጥፎውን ነገር መጋፋት ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡”ስለዚህ ጉዳቱን መጀመሪያ ተመልከቱ፡፡ 
በአጠቃላይ አይነቱ ቢለያይም አፈፃፀሙ ቢቀያየርም መውሊድ ማክበር መጥፎ ፈጠራ ጥመት ስለመሆኑ ከብዙው በጥቂቱ የጠቀስናቸው የቁርአንና የሀዲስ ማስረጃዎች ይበቃሉ::
 መውሊድን መከልከል ነብዩን መውደድ እንጅ መጥላት አለመሆኑን ማወቅ ቢድዓን የሚተገብሩ የሚፈጥሩ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት መቶበት አለባቸው፡፡
 አላህ ቀጥተኛውን መንገድ የመራን የነዚያ በነርሱ ላይ በጎ የዋለላቸውን ሰዎች መንገድ የምንከተል ያድርገን ከተቆጣባቸውና ከተሳሳቱት ሰዎች መንገድ ይጠብቀን፡፡

 ለአለማት ጌታ ለሆነው አላህ ምስጋና ይገባው ሰላትና ሰላም በበላጩ ፍጡር በመቀምቀሚያው ነብይ ላይ ይሁን፡፡ አሚን!!!  

No comments:

Post a Comment