Tuesday, 22 December 2015

ኢስላም፣ጊዜና ሙስሊም

ልብ ያለው ልብ ይበል፣ ዕድሜ የሰከንድ የደቂቃ የሰዓታት የቀናት የወራትና የአመታት ድምር ነው፡፡ “ዘመን ት/ት ቤት ነው፣ቀንና ሌሊት ሲሆኑ ትምህርቱም የህይወት ተሞክሮና ክስተት ነው፡፡” ይላሉ ኡስታዝ አ/ሀሚድ ኪሽኪ፡፡ ዛሬን ከትናንት ተምሮና ተመክሮ ነገ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ቅዱስ ኒያ ማድረግ ለዛሬ ልዩ ራዕይ ነው የትናንቱን ቀን የሚክሱበት ተውባ፡፡ ትናንት በኸይር ይሁን በሸር ውሏችንን መዝግቦ ትንሽ ትልቋን ተግባራችንን ከትቦ የያዘውን ይዞ አልፏል እስከ ቂያማ ቀን ላይመለስ፡፡ ነገ ደግሞ ገና ከእጃችን አልገባም ጨረሩንም አልፈነጠቀም ጣዕም የሌለው ሽታ፡፡
መጨነቅ ያለብን ስለዛሬው ቀን ነው መሮጥ ያለብንም የዛሬዋ ፀሀይ ጋር ነው በሷ ውስጥ ተወልዶ ኖሮና አድጎ ዛሬውኑ እንደሚሞት ሰው፡፡ ሰው ጧት ታይቶ ማታ ጠፊ ነውና እንዴት ራሳችንን እንመን!! “ካመሸህ ንጋትን ካነጋህ ደግሞ ምሽትን አትጠብቅ” ይላሉ ታላቁ ሰሀባ አብደላህ ኢብኑ መስዑድ ( ረ.ዐ) 6 ሰዓት ተውባ እመለሳለሁ አትበል ሩብ ጉዳይ ልትሞት ትችላለህና የሚል መልዕክት ያዘለ ይመስላል አባባላቸው፡፡ ዛሬ ከትናንት ይልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ ለነገው የአኼራ ቤት ዕጩ ለመሆን ራስን ለማዘጋጀት ተስፋው የናኘ እድሉም የሰፋ ነው፡፡ ነገ ዛሬ እስከሚሆን ድረስ ዛሬ በሞቱትም ሆነ ባልተወለዱት ቀናት ላይ ሁሉ አለቃ ነው፡፡ በህይወት ዑደት መዝገበ ቃላት ውስጥ ዛሬ ከሚለው የበለጠ ትልቅ ቃል የለም ቀኑን በአፊያና በሲትር የዋለ ሰው አመሻሽ ላይ ራሱን መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ዛሬ ምን ሰራሁ? የሚለውን ነው፡፡ አዎን በነዚህ በእድሜዬ ቀንሰው፣ ከቆይታዬ ቆርሰው፣ አጀሌን አቃርበው ከሄዱት 12 ሰዓታት 720 ደቂቃዎች 4320 ሰከንዶች ውስጥ ለነፍሴ ምን ሰራሁ? ከአኼራዬ ምን አስቀደምኩ? ለስጋዬስ ምን አተረፍኩ፡፡ይህ ጥያቄ በየቀኑ በጭንቅላቱ ውስጥ መላልሶ ያልደወለ ሰው የጊዜ ጥቅም ያልገባው ለዘላለማዊው ቤቱም ግድ የሌለው ቢሆን ነው፡፡
ለአንድ ሙስሊም ላለውም ሆነ ለሌለው ጊዜ ትልቅ ሀብቱ ናት ይህንን ቱባ ሀብት ሳይጠቀምበት ሙሉ ቀን እንደዋዛ ያለፈው ሰው ቀኑንም ራሱንም የበደለ የጥፋተኞች ጥፋተኛ ነው፡፡ ጊዜ አብረውት ካልተራመዱ በቀር ቆሞ አይጠብቅም ባቡሩም የነቃውን እንጅ የተኛውን ቀስቅሶ አያሳፍርም፡፡ ዱኒያ ሁኔታዋ ሁሉ ጥድፊያ ነው “እንሂድ” “እንሂድ” የሚል ስሜት ወከባና ውዥንብር፡፡ ሩጫዋ ብቻዋን ቢሆን መልካም በሆነ ነበር ነገር ግን ከእድሜያችን እየነጠቀች ትበራለች ሞትንም ወደኛ አቅርባ ትሄዳለች፡፡
መፍጠን መዘግየት መቆም መቀመጥ መተኛት መነሳት መንጋት መምሸት ከዚህ አለም ቁጥር የለሽ ገፅታዎች ከፊሎቹ ናቸው፡፡ ገፅታዋን አጥንቶ ሁኔታዋን ልብ ብሎ በዱኒያ ላይ አጭር ቆይታው በላጩን መርጦ የያዘ ሰው ዛሬም ሆነ ነገ ትርፉ የበዛ ነው፡፡ በሁኔታዋ እንደተገረመና እንደተራገመ ከመቀያየሯ ጋር ራሱን ያላስተካከለ ሰው ወደፊት እንጂ ወደኋላ የማይነፍሰው የጊዜ ነፋስ እንደፈዘዘ ወስዶት እሱንም ከሙታኖች ጎራ የሚቀላቀልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ስለዚህ ሁሌም ከጊዜ አንፃር ንቃት ነው የሚሻለው፡፡ ሙስሊም የዋዛ ፈዛዛ ፍሬ አልባ ጊዜ የለውም ለሱ ሰከንድና ደቂቃም ዕድሜ ናት በሰዓታት ዘርዝሮ ወደ አላህ ይቃረብበታል፡፡ መተኛትም ሆነ መሳሳቱ መማር ይሆን ለዕለቱ ጉርስ መሯሯጡ ለሱ የኢባዳ ዘርፎች ናቸው፣ በአላህ ዘንድ ይተሳሰባል፡፡ በተሠጠው የጊዜ ኒዕማ ያመሰግናል፣ ከጊዜ ጋርም አደብ አለው፣ ቀናትን አይሳደብም ዘመናትን አይራገምም፡፡ ቢወድቅ ቢነሳም ጊዜ አነሳኝ ጊዜ ጣለኝ አይልም፣ የሚያነሳ አላህ(ሱ.ወ) ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አለም ጥድፊያና ውክቢያ ነፃ የሆነ ጊዜ አግኝቶ ለነፍሱ ያልሰነቀ ለስጋው ያልተረፈ ቀናት በሄዱም ቁጥር ይበልጥ ወደ አላህ ያልቀረበ ምንኛ ዕድለ-ቢስ ነው፡፡
ጊዜ ፊደሏ ሁለት ብቻ ሆኖ በሰዎች ዘንድ ዋጋ ብታጣም ተመኗ እጅግ ውድ ነው ወርቅ ቢጠፋብህ ትተካለህ መሬት ቢወሰድብህ ታስመልሳለህ፣ ጊዜ ግን አንዴ ካለፈ አለፈ ነው፡፡ በገንዘብ አትገዛውም በብድር አታገኘውም፣ ሮጠህ አትደርስበትም፡፡ ታዲያ ለምን በጊዜህ ትቀልዳለህ “በ 7 ነገሮች ተቻኮሉ” ይሉናል ነቢያን ( صلى الله عليه وسلم) ሲመክሩን “ምንን
ትጠብቃላችሁ? አላህን የሚያስረሳ ድህነትን፣ በአላህ የሚያኮራ ሀብትን፣ የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ በሽታን ፣ የሚሰባብር (የሚያጃጃ) ሽምግልናን፣ ድንገተኛ ሞትን፣ ቂያማን ወይስ ደጃልን?፡፡” እኮ ምን ትጠብቃላችሁ ጤና፣ ወጣትነትና ትርፍ ጊዜ አላችሁ፣ በኌላ ጊዜ የላችሁም እያንዳንዷ ክፍተት ተጠቀሙ የዲን እውቀትን ጨምሩ፣ በየፌርማታው አንብቡ፣ በየመንገዱ ዘክሩ፣ አላህን በደህና ቀን ተዋወቁ በጭንቅ ጊዜ ይደርስላችኋል፡፡
የጥበብ ጌታ የሆነው አላህ(ሱ.ወ) ወቅቶችን ለኛ በሚመች መልኩ ሰጠን ያወቀበት ለነገ አይቀጥርም ፣ ዛሬ መዋሉን አያውቅምና፣ በበጋ ቤታቸውን ያልተጠባበቁ ክረምት ደርሶ አፈሰሰባቸው የአዝመራውን ጊዜ ያልተጠቀሙ ጊዜው ቢያልፍ ቆጫቸው ደብተራቸውን ሳይከፍቱ የተዘናጉ ፈተና ቢደርስ ጨነቃቸው ከመልካም ስራ ችላ ብሎ ሞት ከች ያለበትም እንዲሁ ነው፡፡
በኢስላም ኢባዳዎች ከጊዜ ሁኔታ ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡ እኛ ፕሮገራም አልባ ሆነን ከዒባዳ ሰዓቶች ጋር አጋጨናቸው እንጅ ሰላትም ሆነ ሌሎች የአምልኮ ስርዓቶች ከጥናትም ሆነ ከስራ አያዘናጉም፣ ከእያንዳንዱ እንቅስቃሴ በኋላ የማረፊያ ሰዓታት ቢሆኑ እንጅ፡፡ ሙስሊም ዲኑን ትቶ ለዱኒያ ብቻ አይኖርም፣ ባሪያነቱ ለአላህ ነው፣ ዱኒያን ትቶም ዲኑን ብቻም አያዘወትርም ኢስላም ባህታዊነትን አይደግፍም፡፡ “ሰዓተን ሊነፍሲከ ወሰዓተን ሊረቢከ” “ከፊሉን ሰዓት ለራስህ ከፊሉን ደግሞ ለጌታህ” ነቢያችን ( صلى الله عليه وسلم) አስተምረውናል፡፡
የነቢዩን ትልቅ ምሳሌ ሰምተን ለሁሉም የድርሻውን ከሰጠን ነፍሳችንንም ሆነ ስጋችንን አንበድልም ከአላህም አንጣላም፡፡ ነገሮችን ከአላህ ፈቃድ ውጪ በራስ ጉልበትና ጥረት ብቻ ለማስኬድ መሞከር ውጤት የለውም፡፡ በሰራነውና ባጠናነውም የሚባርክልን በያንዳንዷ የህይወት ክፍላችን ውስጥ አላህን ያስገባን እንደሆነ ነው፡፡ በትንሿ ጥረታችን መሐል አረፍ ብለን “ጌታችን ሆይ! አንተ ያገራሀው ካልሆነ ገር የለም፣ አንተ ከባዱንም ነገር ታገራለህ፤ መመካታችን ባንተ ነው፤ አንተ ምንኛ ያማርክ መጠጊያ ነህ” ካላልን የምናውቀውም ይጠፋብናል፣ የያዝነውም ይወድቅብናል፡፡ ቁም ነገሩ ለረጅም ሰዓታት ማንበብ/መስራት በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበር ብቻ አይደለም፤ አላህ የባረከላቸው በሱም እርግጠኛ መተማመንን የተማመኑ ሰዎች በትንሽ ጊዜና ጥረት ትልቅ ውጤት አሳይተውናል፡፡ስለዚህ ለስጋችን ብለን ነፍሳችንን አንበድል፡፡ ከጀማዓ ሰላትም አንቅር፣ ሌባ ማለት ንብረት በድብቅ የሚሰርቅ፤ የሰውን ኪስ የሚያወልቅ አይደለም፡፡ሌባ ማለትስ ለራሱ ጉዳይ ብሎ ከዒባዳ ሰዓቶች የሚቀናንስ ወደ ሰላትም ከገባ በኋላ የሰላትን ሩኩዕና ሱጁድ የሚቆርጥ የሚቆራርስ ነው፡፡ እኛ ባናውቅ ባይገባን ነው እንጅ መጥፋቱ የማይቆጭ ጊዜ ቢኖር ለአላህ ብለው ያጠፉት ነው፡፡ትክክለኛ እድሜያችንም በሱ ዒባዳ ላይ ያሳለፍነው ነው፡፡

No comments:

Post a Comment